የኩላሊት ህመም ምንነት እና መፍትሔው
By Sahle relation
ኩላሊቶቻችን በታቸኛው ጀርባችን ከጎድን አጥንታችን በታች የሚገኙ ሁለት ባቄላ መሰል አካሎች ናቸው። ኩላሊቶቻችን ደማችንን የማጣራት ስራ ሰርተው ቆሻሻውን በሽንት መልክ እንዲወገድ ያደርጋሉ። የኩላሊት ሌላኛው ጥቅም ሰውነታችን ውስጥ የሚገኝ የማያስፈልግ ውሃ ማስወገድ ነው። ሰውነታችን ውሃ ሲያስፈልገው በማጠራቀም ይታወቃሉ። በተጨማሪም ሰውነታችን ውስጥ ያለውን የካልሲየም እና ፎስፌት መጠን ይቆጣጠራሉ። የደም ግፊት የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖችንም በማመንጨት ይታወቃሉ።
በጤንነት ለመቆየት የኩላሊቶቻችንን ጤንነት መጠበቅ አለብን። የኩላሊት ህመም ከሚያመላክቱ ስሜቶች መሃከል የሽንት ቀለም መቀየር፣ የሽንት ብዛት መቀየር፣ የማዞር ስሜት፣ ማስመለስ፣ የደም ማነስ፣ የመተንፈስ ችግር፣ የመቀዝቀዝ ስሜት፣ የድካም ስሜት፣ ቆዳን ማሳከክ እና የተለያዩ የህመም ስሜቶች ይገኙበታል።
የሰው ኩላሊትን የሚጎዱ 10 ልማዶች
ሽንትን መቋጠር፣ በቂ ውሃ አለመጠጣት፣ ጨው ማብዛት፣ ፔይን ኪለር(ህመም የሚቀንሱ) መድሃኒቶችን መጠቀም ማዘውተር፣ ፕሮቲን ያላቸው ምግቦች ማብዛት፣ መጠጥ ማብዛት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ ቡና መጠጣት፣ ቀላል ኢንፌክሽኖችን በግዜው አለመከታተል እና የእንቅልፍ እጦት ለኩላሊት በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸዉ፡፡ ምንጭ ጤና ሚኒስቴር