የማህበረሰብ ውይይት

By Sahle relation

የማህበረሰብ ውይይት

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት የማህበረሰቡ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

ሆስፒታሉ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከአካባቢው ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የማህበረሰብ ውይይት አካሄደ።

በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ አሰፋ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ውይይቱን አስጀምረዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራአስኪያጅ ዶክተር አብድረሂም በድሩ የሆስፒታሉን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ያለበትን የአገልግሎት አሰጣጥ እና እየተሰጡ ያሉ የህክምና አገልግሎቶችን በተመለከተ ከውይይቱ በፊት አቅርበዋል፡፡

ዶክተር አብድረሂም በገለፃቸው ሆስፒታሉ ስራ ከጀመረ ሶስት አመት ሲያስቆጥር አሁን ያለበትን ደረጃ ላይ ለመድረስ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው ካሁን በፊት አገልግሎት መስጠት ባልጀመረባቸው የህክምና አገልግሎቶች ባሳለፍነው 2014 በጀት አመት በማስጀመር ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የአእምሮ ህሙማን ተኝቶ ህክምና በስፔሻሊቲ ደረጃ አገልግሎት መስጠትን፣የጨቅላ ህፃናት የቀዶ ህክምና ማስጀመርን፣ የጨቅላ ህፃናት ህክምና ክፍል በተሻለ ደረጃ በማደራጀት አገልግሎት ማስቀጠልን፣ የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት በጉብርየ ክፍለ ከተማ መከፈቱን እና ሌላው የስፔሻሊቲ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ከማንሳት ባሻገር የማህበረሰቡን የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ ብሎም ማህበራዊ የህይወት እንግልትን የቀነሰበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው ሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት መስጠት ባልጀመረባቸው አገልግሎቶች በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በትኩረት እንደሚሰራበትም ጠቁመዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሆስፒታሉ ስራ ከጀመረ ያሳያቸው ለውጦች ይበል የሚያሰኝ መሆኑን በመጥቀስ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከተነሱ ሃሳብ አስተያየቶች መካከል በዋናነት የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት አለመጀመሩን፣ ታካሚ ወደ ሆስፒታሉ በመጣ ሰዓት መጉላላትን፣የህክምና ማሽኖችን እንደ ሲቲ ስካን ያሉ የህክምና የግብዓት እቃዎች እስካሁን አለመቅረቡን፣ሽንት ቤቶች ላይ የንፅህና ጉለትን መኖሩን፣ የሪፈር መጠን አለመቀነስን፣ የመድሃኒት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመኖሩን ፣ ከባለሙያ ስነ - ምግባር እና ከሰው ሃይል ቅጥር እንዲሁም በሌሎች የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጥያቄዎችና አስተያየቶች አንስተው በሆስፒታሉ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በማህበረሰብ ውይይቱ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር፣ከጉብርየ ክፍለ ከተማ፣ከእምድብር ከተማ ፣አገና ከተማ፣ የተውጣጡ የማህበረሰብ አካላት፣ የሆስፒታሉ ከፍተኛ አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

Search articles

Recent articles

    Loading...