“የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ጋር በዛሬው እለት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

By Sahle relation

“የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ጋር በዛሬው እለት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ግንቦት 7/2017ዓ.ም.

“የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ጋር በዛሬው እለት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር የጤና ባለሙያዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ የህልውና ማስከበር ዘመቻ ባደረገችበት፣ ኮቪድ በተከሰተበት እንዲሁም የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች በተከሰቱበት ጊዜ ለህይወታቸው ጭምር ሳይሳሱ ሀገራችን የገጠማትን ፈተና በግንባር ቀደምትነት እና በጽናት በመጋፈጥና ሰብአዊነት በተሞላው ወገናዊ ሃላፊነት ጭምር ላበረከቱት ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ፍቅረጽዮን ደገሙ “የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ሰነድ ለተሰብሳቢዎቹ አቅርበዋል፡፡ ዶክተር ፍቅረጽዮን በዋናነት ትኩረት ያደረጉት ጤናው ዘርፍ ያለበት ሁኔታና የባለድርሻ አካላት ሚና፣የጤና የሰው ሀብት ልማት፣ በጤናው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ችግሮች በሚሉ ነጥቦች መነሻ ላይ በማተኮር ሰነዱን አቅርበዋል፡፡

በሰነዱ ዙሪያ የጤና ባለሙያዎቹ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እና ትኩረት የሚሹ ሃሳቦችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ካነሷቸው ነጥቦችም ዋናዎቹ ዩኒቨርሲቲው የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው በቀጣይ ሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው ጥረቱን ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አሁን ላይ እንደሀገር የተሚታየውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም በማይችሉበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን በዝርዝር ገልጸው መንግስት የደሞዝ ጭማሪ በማድረግ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ላይ ይበልጥ ትኩረት በመስጠት ጥያቄዎቻቸውን ለመፍታት አጽንኦት ተሰጥቶ እንዲሰራበት ገልጸዋል፡፡

አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል የጉራጌ ዞን የመንግስት ተጠሪ በበኩላቸው እንደገለጹት የጤና ባለሙያዎች በመድረኩ ላይ ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸው በመወያየት፣ በሰለጠነ ሁኔታ በመነጋገር ተቀራርበን ልንፈታቸው የምንችላቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸው በአንጻሩ ግን የተለየ አጀንዳ ባላቸው አካላት መልካም ሃሳቦቻቸው እንዳይጠለፉ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባው ገልጸው በቀጣይ ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል ፡፡

አቶ ማሙሽ ሁሴን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎቹ እጅግ በሳልና በሰከነ መንገድ እንዲሁም ፍጹም ስነ-ምግባር በተሞላ መልኩ ላቀረቡት ጥያቄ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ከዞኑና ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጥምረት መስራት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

አቶ አየለ ፈቀደ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ በበኩላቸው ለጤና ባለሙያዎቹ ላቀቡት አስተያየት ያላቸውን አድናቆት ገልጸው በቀጣይ መሰል የውይይት መድረኮችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ በመቀናጀት እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በተነሱት ነጥቦች ዙሪያ ከመድረክ የማጠቃለያ ሃሳብ የተሰጠ ሲሆን በማጠቃለያ ሃሳቡ ላይ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል የዞኑ የመንግስት ተጠሪ እንገለጹት በተሰማሩበት የጤናው ዘርፍ በሙያቸው ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ያሉት ባለሙያዎቻችን ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸው ጥያቄአቸውን ያቀረቡበት መንገድ ቀና እና አዎንታዊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው በማጠቃለያው ላይ እንደገለጹት ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰቡ ጥያቄ መነሻነት በጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ተጀምሮ የነበረው ሆስፒታል በማስጨረስ አቅም በፈቀደ መጠን ግብአቶችን በማሟላት በሆስፒታሉ አማካይነት የሚገለገሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን የጤና ችግር ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው በቀጣይ የሆስፒታሉን አገልግልሎት አሰጣጥ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በጽናት እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ አያይዘውም የጤና የዘርፉን ሁለንተናዊ አፈፃፀም ለማሻሻል መሠል የውይይት መድረኮች በተለያየ ደረጃ እንደሚቀጥል በማጠቃለያቸው ላይ አብራርተዋል።

በመጨረሻም ዘርፉን ከማሻሻል አንጻር በቀጣይ በሚደረጉ የውይይት መድረኮች ላይ የጤና ባለሙያዎቹን በመወከል የሚሳተፉ 20 ተወካዮች በተሰብሳቢዎቹ አማካይነት ተመርጠዋል፡፡

ለጥበብ እንተጋለን!

We Strive for Wisdom!

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

Search articles

Recent articles

    Loading...