በአጥንትና መገጣጠሚያዎች ላይ የሚያጋጥሙ ውስብስብ የጤና ችግሮችን መቅረፍ እና ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት
By Sahle relation

ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ለሚያጋጥማቸው የአካል ጉዳት የጤና እክል በተገቢው መንገድ ማከም እንዲቻል ባህላዊ የአጥንት ህክምና ባለሙያዎች ፣በተለያዩ የጤና ተቋማት ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች እና ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ቦሳድ የጥናትና የምርምር ቡድን በኢትዮጵያ ከአጥንት እና መገጣጠሚያ ሃኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር በቡታጅራ ከተማ ከመጋቢት 25 - 27/2018 ዓ.ም ለ3 ቀናት የቆየ የምክክር መድረክና ስልጠና ሰጥቷል።
ቦሳድ ሃገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ቡድን በሃገራችን በተለምዶ ከሚከሰቱ የአጥንት እና መገጣጠሚያ ጉዳቶች ጋር በተያያዘ በሚመጡ የተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ከዘመናዊ የህክምና ሳይንስ ጋር በማጣጣም የተለያዩ ሙያዊ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። በሃገራችን ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆንም በጋራ እየሰራ ስለመሆኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአጥንት ህክምና ጥንቃቄ ካልተደረገለት ለውስብስብ የጤና ችግር የሚያጋልጥ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ሲያነሱት ይስተዋላል።
በስልጠና መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የምስራቅ ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ በአጥንትና መገጣጠሚያዎች ላይ የሚያጋጥሙ ውስብስብ የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ እና ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችል በባህላዊ መንገድ የሚሰጡ ህክምናዎች ዘመናዊ የህክምና ሳይንስ መርሆዎችን በተከተለ እና በማይጣረስ መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። ዘመናዊ ህክምና ከመሰጠቱ አስቀድሞ ሃገር በቀል እውቀትን መሰረት በማድረግ ባህላዊ የአጥንትና የመገጣጠሚያ ህክምና ሲሰጥ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰለሞን ተጠያቂነት ያለበት አሰራር ለመዘርጋት እና ወቅቱ የደረሰበትን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በዘመናዊ የህክምና ሳይንስ መደገፍ ይገባልም ብለዋል።
ባህላዊ የአጥንት ስብራትና ውልቃት ህክምና የሚሰጡ ወጌሻዎች ተጠያቂነት ባለው መልኩ ስራዎችን በመስራት ማህበረሰቡ ላይ በስፋት እየተከሰተ ያለውን የአካል ጉዳተኛነት እንዲቀንስ ለማድረግ በእንደዚህ እና መሰል ፕሮግራሞች የምክክርና ስልጠና መድረኮች ላይ መገናኘት በቅርበት ለመስራት ይህ አይን ገላጭና የመጀመሪያ መድረክ ነው ብለዋል።
በመድረኩ በዘመናዊና በባህላዊ የአጥንትና የመገጣጠሚ እንዲሁም የውልቃት ህክምና መካከል ያሉ ችግሮችን በተመለከተ የተለያዩ ወርክ ሾፖች በዶክተር አብረሃም ገብሬ ፣ በዶክተር እንየው ጌታቸው እና ዶክተር ሰለሞን አልማው ቀርበው በተሳታፊያን ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአጥንትና መገጣጠሚያ ትምህርት ክፍል የፕሮጀክቱ ስልጠና አስተባባሪዋ ዶክተር ፍቅር አውራሪስ በበኩላቸው የባህላዊ የአጥንት ህክምና አግኝተው ለተወሳሰቡ የጤና ችግር የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ዘመናዊ ህክምና እንዲያገኙ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ግንዛቤ መፍጠር የቦሳድ አላማ መሆኑን ገልጸዋል።
በ8 ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ማህበረሰብ ተኮር ጥናት በማድረግ በባህላዊ ህክምና ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት ለማህበረሰቡ ማመላከት እና ጉዳቱን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ፍቅር ተናግረዋል።
ባህላዊ አጥንት ህክምና ለማህበረሰቡ የሚሰጡ ወጌሻዎች ጥንቃቄና ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንዲሰሩ ከዛ አለፍ ሲልም ወደ ህክምና ተቋም እንዲሄዱ ግፊት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም የፕሮጀክቱ ስልጠና አስተባባሪዋ አስረድተዋል።
ባህላዊ ህክምና ከሚሰጡ ባለሙያዎች እርስበርስ የመታዋወቅና ተግባራቸውን ከዘመናዊ ህክምና ጋር አስተሳስሮ መስጠት እንዲቻል መስል የምክክር መድረኮችና ስልጠናዎች ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአጥንትና የመገጣጠሚያ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሃኪም ዶክተር አብረሃም ገብሬ ናቸው።
በመድረኩ የተገኙት የባህላዊ ህክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች (ወጌሻዎች) በሰጡት አስተያየት ስልጠናው መካሄዱ በሙያው ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለሙላት እድል የሚፈጥር ስለመሆኑ አንስተዋል። ታካሚዎች አገልግሎት ለማግኘት ሲመጡም በአቅም ልክ ህክምና መስጠታ ከአቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ተጨማሪ የጤና ጉዳት እንዳያስከትል ወደ ዘመናዊ ህክምና ተቋም መላክ ከኛ ይጠበቃልም ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
በስልጠናው ከተለያዩ የጤና ተቋማት የመጡት ባለሙያች እንደገለፁት ስልጠው የባለሙያውን የሙያ ክፍተት በእጅጉ የሚሞላና ትልቅ ግንዛቤ የፈጠረላቸው እንደሆነ አንስተዋል። እነሱ ያገኙትን ስልጠናም ወደየተቋማቸው ወስደው ሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር ተቀናጅተ በመስራት የአጥንት ስብራትና ውልቃት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱት ችግሮች ለመቀነስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል ።
በመጨረሻው ቀን ለአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሳነ መምህራን ተመሳሳይ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የምስራቅ ጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ አቶ ሰልማን እንደገለፁት ቢሮው ትምህርት ቤቶቻችን የህፃናት አደጋ ለመቀነስ ምቹ ከባቢ በመፍጠር አጠናክሮ በመስራት ጉዳቶችን መከላከልና ከተከሰቱም ምን ምን አድርጎ ወደ ጤና ተቋማት መላክ እንዳለብን ስልጠና ግንዛቤ ስለሚፈጥር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመድረኩም ተሳታፊዎ ትልቅ ግንዛቤ የፈጠረላቸው እንደሆነ ወደየትምህርት ቤቶቻቸው ሲመለሱም ለመምህራን ለተማሪዎችና ለተማሪ ወላጆች በተለያዩ መንገዶች በማጋራት እንደሚሰሩበት ገልፀዋል። የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ መስጫ ቁሳቁሶችን ማሟላትና ቀይ መስቀል ክበብን በማጠናከር በቀላሉ የቦሳድን አላማ ማሳካት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።
