የእውቀት፣የክህሎት እና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስልጠና
By Sahle relation

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ለግቢ የጥበቃ ፖሊስ የእውቀት፣የክህሎት እና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስልጠና ሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ በተቋሙ ውስጥ ለሚሰሩ የጥበቃ ፖሊሶች በተሰማሩበት የስራ መስክ ላይ በትኩረት እና በትጋት ሃላፊነታቸውን በመወጣት መስራት እንዲችሉ የሚያግዛቸው ስልጠና መሆኑን በዕለቱ ስልጠናውን የሰጡት የሆስፒታሉ የሰላም እና ደህንነት አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ በሃሩ አለሙ ገልፁ፡፡
የጥበቃ ፖሊሶች የሚጠበቅባቸውን ስራ ሁሉ በመስራት፣የተቋሙ ንብረት እና የሰራተኛውን ደህንነት በመጠበቅ በኩል ሃላፊነታቸው መወጣት እንደሚጠበቅባቸው በስልጠናው ተጠቅሷል፡፡ ሌላው ወደ ተቋሙ የሚገቡ ንብረቶች እንዲሁም ከተቋሙ የሚወጡ ማንኛውም አይነት ንብረት እና የተለያዩ እቃዎችን መቆጣጠርና የተቋሙን ንብረት በመለየት ልዩ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም የጥበቃ ፖሊስ ለአገልግሎት ፈላጊው ማህበረሰብ መልካም ስነ-ምግባር በማሳየት እና በታጋሽነት ደንበኞችን በተገቢው ሁኔታ እና ተቋሙ በሚያዘው መመሪያ መሰረት ማስተናገድ እንደሚጠበቅባቸውም ተገለፀ፡፡
ስልጠናውን የወሰዱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሰጡት ሃሳብ አስተያየት በሚሰሩት የጥበቃ ስራ ክፍተቶች እንዳሉባቸው በማንሳት በቀጣይ ግን ተቋሙ የእኔ እና የቤተሰቤ ነው በሚል የባለቤትነት ስሜት ለመስራት መወሰናቸውን ገልፀዋል፡፡